
በስልጤ ዞን የሳንኩራ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት በሁሉም የወረዳው የትምህርት ተቋማት ለልማት መዋል የሚችሉ መሬቶች ለልማት እንዲውሉ በማስቻል ትምህርት ቤቶች የውስጥ አቀማቸውን በማሳደግ ውጤታማ የመማር ማስተማር ስራን ማከናወን እንዲችሉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል ፡፡
በዚህም መሰረት በወረዳ ደረጃ የትምህርት ቤቶችን የውስጥ አቅም ለማሳደግ በመደበኛ መኸርና በልግ እንዲሁም በፍራፍሬ ልማት ተቋማት በስፋት እንዲያለሙ እየተሰራ ሲሆን በዚህ ረገድ የታች ቀሞ አንደኛ ደረጃ እና የጃታ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በዛሬው ዕለት ሁለቱ ተቋማት ለመማር ማስተማር ስራው እንዲረዳቸው የውስጥ አቅማቸውን ለማሳደግ በተቋማቱ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች ላይ ምልከታ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በወቅቱም በበልግ ልማት የለሙ የቦቆሎና የቦለቄ እንዲሁም በፍራፍሬ ልማት ደግሞ ፤ የፓፓዬና አቡካዶ ልማቶችን በስፋት መመልከት ችለናል፡፡
አቶ አብዲ የሱፍ የጃታ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ርዕሰ መምህር ፤አቶ
መሀመድ ከድር ደግሞ የታች ቀሞ ቀበሌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሲሆኑ የትምህርት ተቋማቸውን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ነግረውናል ፡፡
ርዕሰ መምህራኖቹ በየጊዜው ገቢያቸውን ለማሳደግ የግብርና ልማቶች ስራዎችን የሚሰሩ እንደሆነና ይህም የትምህርት ቤቶችን ስታንዳርድ ሟሟላት እንዲችሉና ለመማር ማስተማር ስራው የሚረዱ ግብዓቶችን ማቅረብ እንዲችሉ እያስቻላቸው መሆኑን ገልጸው አሁን ላይ በስፋት የፍራፍሬ ልማትን በተቋማቸው ተግባራዊ እያደረጉ ስለመሆኑና የሚደርሱ ፍራፍሬዎችንም ውለው እያደሩ ለሚማሩና ለሚያስተምሩ መምህራን እንዲጠቀሙ እየተደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል ፡፡
በትምህርት ልማት ዘርፍ የሚስተዋለውን የውጤታማነት ችግር መቅረፍ የሚቻለው የትምህርት ተቋማትን የውስጥ አቅም ማሳደግ ሲቻል መሆኑን የገለፁልን የሳንኩራ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ደረጀ ራህመቶ በወረዳው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በቅጥር ጊቢያቸው የሚገኙ ባዶ ቦታዎች በሙሉ ገቢ ማስገኘት ለሚያስችሉ የልማት ስራዎች መዋል እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል ፡፡
ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር ተግባራዊ ማድረግ እዲችሉና የትምህርት ተቋማትም የውስጥ ገቢያቸውን ማሳደግ እንዲችሉ በየትምህርት ቤቱ የፍራፍሬ ማዕከል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያስረዱት አቶ ደረጀ በተያዘው የበጀት ዓመት በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከ80 ሄ/ር መሬት በላይ እንዲለማ ስለመደረጉ ጠቅሰው በየጊዜው በሚሰሩ የልማት ስራዎች የሚገኙ ገቢዎች ትምህርት ቤቶች የውስጥ አቅማቸውን እያጠናከሩበት ይገኛል ብለዋል፡፡
አቶ ደረጀ አያይዘውም በቀጣይ በትምህርት ተቋማት የሚገኙ መሬቶች ለመምህራን በሚል ውለው እያደሩ የሚያስተምሩ መምህራኖች አልምተው መጠቀም እንዲችሉ በማደረግ የትምህርት ተቋማት ለመማር ማስተማር ስራው ውጤታማነት ምቹ ከባቢ መሆን እንዲችሉ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል፡፡